ሰለ ካውንስሉ
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል በአዋጅ ቁጥር 1208/2012 ተቋቁሟል፡፡
ካውንስሉ ለምን ተቋቋመ?
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች ቤተ እምነቶች፤ ኅብረቶችና የቤተ ክርስቲያን አጋዥ ድርጅቶች (Ministries) ቀደም ባሉት ዘመናት በወንጌል ስርጭት በኩል ከፍተኛ አገልግሎት የሰጡና ፍሬያቸውም ጎልቶ የሚታይ ቢሆንም በተደራጀ መንገድ ተቀራርበው ቢሠሩ የላቀ ውጤት እንደሚገኝ በመገንዘባችን፤
የጋራ ጉዳዮቻችንን በአንድ ድምጽ የሚያስተጋባ አደረጃጀት ማስፈኑ በመንፈሳዊም ሆነ በአገራዊ አገልግሎታችን ውጤታማና ተጽዕኖ ፈጣሪ ለመሆን ያስችለናል ብለን ስለምናምን፤
በአገሪቱ ሕገ መንግስት የተከበሩልንን መብቶች በአግባቡ መፈጸማቸውን የሚከታተልና ለተግባራዊነታቸውም የሚሠራ የጋራ ተቋም መዘርጋቱ የሚያስገኘው አዎንታዊ ጥቅም ከፍተኛ በመሆኑ፤
የጋራ አደረጃጀት በመካከላችን የሚከሰቱ አለመግባባቶችን እንደ እግዚአብሔር ቃል በፍቅር ለመፍታት መልካም ዕድል የሚሰጥና ምሳሌነታችንም ጎልቶ እንዲታይ የሚያስችል ሆኖ በማግኘታችን፤
በአገራችንም ሆነ በዓለም ዙሪያ በየጊዜው ለሚነሱ ተግዳሮቶችና ከክርስትና አስተምህሮ ጋር ለሚጋጩ አመለካከቶች በተቀናጀ መንገድ ምላሽ ለመስጠትና ምዕመናንም በእምነታቸው ጸንተው እንዲቆሙ ለማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በማግኘታችን፤
አገራችን በየጊዜው የሚገጥሙዋት የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች የሚቃለሉበት፤ ግጭቶች የሚፈቱበትና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈንም የሚደረገው ጥረት ውጤታማ የሚሆንበትን ሥራ ለመሥራት በጋራ መንቀሳቀሱ የሚያስገኘው ውጤት ከፍተኛ ስለሆነ፤
ከፖለቲካ፤ ከኢኮኖሚና ከማኅበራዊ አገልግሎቶች ጋር ተያይዘው በሚነሱ ጥያቄዎችና ተቃውሞዎች ምክንያት ኅብረተሰቡ ግጭት ውስጥ እንዳይገባ ለመከላከል፤መከባበርና መደማመጥ እንዲኖር ለማስተማርና ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት በጋራ መንቀሳቀሱ መለኮታዊ ኃላፊነታችንን ለመወጣት እንደሚያስችል በማመን የወንጌል አማኞች ቤተ እምነቶች እና አብያተ ክርስቲያናት ኅብረቶች ለኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል በአዋጅ ቁጥር 1208/2012 ተቋቁሟል፡፡