አዕማድ እምነቶች (አስተምህሮ)
ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የወንጌል አማኞች ዋና ዋና የእምነት ምሶሶዎች መሠረታዊያን በመሆናቸው ወሳኞችና ዐበይት አስተምህሮ ናቸው፡፡
የካውንስሉ የእምነት መሠረት በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኳ የተጻፈው የመጀመሪያይቱ የሐዋርያት ቤተክርስቲያን እምነት ነው፡፡ ስለዚህ የወንጌል አማኞች ጥንታዊያኑ ታሪካዊያኑ የቤተክርስቲያን ጉባኤያት ያወጧቸውን፡- የሐዋርያት፣ የኒቂያ፣ የአትናቴዎስና የኬልቄዶን የእምነት መግለጫዎች ተቀብለው በየዘመኑ የተነሱ ተሐድሶዓውያን ወደ ቀደመው መጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነትና አስተምህሮ ለመመለስ ያደረጉትን ጥረቶች አካትተው የቆሙ ናቸው፡፡ በዚህ መሠረት ካውንስሉ “አምስቱ ብቻዎች” በመባል የሚታወቁትን “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” “ክርስቶስ ብቻ” “በጸጋ ብቻ” “በእምነት ብቻ” እና “ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ” እንዲሁም ከእነርሱ ጋር የሚጠቀሰው “የአማኞች ሁሉ ክህነት” የተባለውን አስተምህሮ ይቀበላል፡፡
ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የወንጌል አማኞች ዋና ዋና የእምነት ምሶሶዎች መሠረታዊያን በመሆናቸው ወሳኞችና ዐበይት አስተምህሮ ናቸው፡፡
አዕማድ 1. መጽሐፍ ቅዱስ – ቃለ እግዚአብሔር
ካውንስሉ ስድሳ ስድስቱን የብሉይና የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የያዘውን መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር እስትንፋሳዊ ቃል፤ የአማኞች የእምነታቸውና የምግባራቸው ዋና መመሪያና የመጨረሻ ባለሥልጣን እንዲሁም ማዕከል እንደሆነ ያምናል፤
መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው፤የእግዚአብሔር መገለጥ ነው፡፡ በቅዱሳን ሰዎች አማካኝነት የተጻፈ ቢሆንም በመንፈስ ቅዱስ መሪነትና ተቆጣጣሪነት የተጻፈ ነው፡፡ ስለዚህ በውስጡ የተካተቱት እርስ በርስ የተያያዙትና የሚቀባበሉት ሁለቱም ኪዳናት የሚያስተምሩት ትምህርት ስህተት አልባና የማይሻር ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከሰው የአእምሮ እውቀትና አመክንዮ ችሎታ በላይ ከግለሰቦች ገጠመኞችና ልምምዶች በላይ እንዲሁም ከቤተክርስቲያን ወግና ልምምድ በላይ የላቀ ሥልጣን ያለው፤ሊቀነስበት ወይም ሊጨመርበት ያልተፈቀደ፤ ቤተክርስቲያንን በእውነቱ ሥልጣን የሚመራ ቃል ነው፡፡ በቤተክርስቲያን የታሪክ ሂደት ልዩ ልዩ የትርጓሜ ወይም የሥነ-አፈታት መስመሮች ቢከሰቱም እውነተኛ የአተረጓጎም ሂደት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የተጻፈበትን ዐውድ ያገናዘበ ከአሁኑ ዘመን ጋር ያለውን ተዛምዶ ያጤነ እና በመንፈስ ቅዱስ አብርሆት የሚደገፍ መሆን እንዳለበት ካውንስሉ ያምናል፡፡
(ምሳ 30፡6፤ ሉቃ 4፡18-2፤1ጢሞ 5፡18፤ 2ጢሞ 3፡16፤ 2ጴጥ 1፡20-21፤ 2ጴጥ 3፡15-16፤ ዕብ1፡1-2 ዕብ 4፡12፤ ራዕ.22፡18-19፤)
አዕማድ 2. እግዚአብሔር አሀዱ ወሥሉስ አምላክ
ካውንስሉ በሦስት አካላት (persons) በሚኖር አንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ፤ በእግዚአብሔር ወልድ፤ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ያምናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረቱ በሆነው ርቱዕ ክርስትና የሚስጥረ ሥላሴ አስተምህሮ መሠረት እግዚአብሔር አንድ ነው፡፡ ከዘላለም ጀምሮ፤ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ተብለው በሚጠሩ ሦስት አካላት ይኖራል፡፡ እያንዳንዱ የሥላሴ አካል ፍጹም አምላክ ነው፡፡
እግዚአብሔር በሦስት አካላት ይኖራል ስንል ሦስት አማልክት ወይም መለኮቶች አሉ ማለት አይደለም፡፡ “ሦስት” የሚለው ቃል ‹ስምን›‹ግብርን›‹አካልን› የሚያመለክት ሲሆን አንድ የሚለው ቃል ደግሞ ‹ባህርይን› ‹መለኮትን› እና ‹ሕልውናን› ያመለክታል፤ ስለዚህ ካውንስሉ በአሀዱ ወሥሉስ አምላክ (በሥላሴ) ያምናል፡፡
(ዘፍ 1፡26፤ ዘዳ 4፡35፤ ዘዳ.6፡4፤ 1ዜና17፡20፤ ማቴ. 3፡16፣ 28፡19፤ 1ቆሮ 8፡4-6፤ 2ቆሮ13፡14፤ 1ጢሞ 1፡12)
ሀ/ እግዚአብሔር አብ
ካውንስሉ እግዚአብሔር አብ የሁሉ ፈጣሪ፣ እውቀቱና ችሎታው የማይወሰን፣ በፈቃዱ ሁሉን የሚመራ፣በሰማይና በምድር የወደደውን የሚያደርግ፤ ከልካይም ፈቃጅም የሌለው ልዑል አምላክ እንደሆነ፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን እና በፍጹም ቅድስና የሚኖር በፍቅር የተሞላ፤ ታማኝና መሃሪ አምላክ እንዲሁም ዘላለማዊ መሆኑንና ዓለምን ለማዳን አንድ ልጁን ወደ ዓለም የላከ አዳኝ እንደሆነ ያምናል፡፡
(መዝ 24፡1፤ ኢሳ 45፡5-10፤ ዳን 4፡35 ማቴ 10፡29፤ ዮሐ 1፡18፣ 3፡16፤ ሐዋ 3፡25-26፣ 17፡26፤ 1ጢሞ 6፡15-16፤ ኤፌ 1፡1፤ 1ዮሐ 1፡18)
ለ/ እግዚአብሔር ወልድ (ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ)
ካውንስሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብ አንድያ ልጅ፤ ከአብ ጋር ለዘላለም የኖረ አምላክ፤ ዓለም በእርሱ በኩል የተፈጠረ፤ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በሥጋ ከድንግል ማርያም የተወለደ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው ሆኖ (መለኮቱና ትስብእቱ ሳይዋዋጡና ሳይከፋፈሉ) ሁለቱን ባህርያት በአንድ አካል የያዘ፤ በምድር ላይ ያለ ኃጢአት የኖረ፤ ወንጌል እየሰበከ፤ ድውያንን እየፈወሰ፤ ሙታንን እያስነሳ፤ በጎ ሥራ እያደረገ የተመላለሰ፤ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል መካከለኛ የሆነ፤ስለ ሰው ልጆች ኃጢአት ቤዛ ሆኖ በመስቀል ላይ የሞተ፤በሦስተኛው ቀን በኃይልና በክብር ከሙታን የተነሳ፤ወደ ሰማይ በክብር ያረገ፤ በአባቱ ቀኝ ተቀምጦ ስለ እኛ የሚማልድ፤በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ በመላእክት ታጅቦ በክብርና በግርማ ወደ ምድር ተመልሶ የሚመጣ እንደሆነ ያምናል፡፡
(ማቴ 1፡20-21፤ ሉቃ 2፡5-7፣ 3፡16፤ ዮሐ1፡14-18፣ 6፡68-69፣ 8፡58፤ 1ቆሮ 1፡30፤ ቆላ 1፡1-4፣ 3፡1፤1ጢሞ 2፡5፤3፡16፤ 1ዮሐ 1፡1-3፤ዕብ 13፡8)
ሐ. እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ
ካውንስሉ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ጋር የተካከለ አምላክ መሆኑን፤በሁሉ ቦታ የሚገኝ ፈጣሪ መሆኑን፤ አማኞችን ወደ እውነት ሁሉ የሚመራ፤የሚያጽናና፤እንደ ፈቃዱም የጸጋ ስጦታዎችን ለምዕመናን የሚሰጥ፤በእነዚህ ስጦታዎቹ አማካኝነት በሁሉ ዘመን እየሠራ ቤተክርስቲያንን የሚያንጽ፤ስለ ክርስቶስ የሚመሰክር፤ዓለምን ስለኃጢአት፤ስለ ጽድቅ፤ስለ ፍርድ የሚወቅስ መሆኑን ያምናል፡፡ አማኞች በኃጢአት ሲመላለሱ መንፈስ ቅዱስ ማዘኑን፤ስለዚህ አማኞች በሕይወት ንጽሕና እንዲኖሩ መንፈስ ቅዱስ ጸጋ እንደሚሰጣቸውና ለአገልግሎታቸውም ኃይልን እየሰጠ ወደ መንፈሳዊ ሕይወት ሙላት እንደሚያሳድጋቸውም ያምናል፡፡
(ኢዮ 33፡4፤መዝ.139፡7-10፤ዮሐ 14፡ 15-16 ፡26፤ ዮሐ 15፡26)
አዕማድ 3. የሰው ማንነት ሁኔታ
ካውንስሉ ሰው በእግዚአብሔር አምሳል መፈጠሩን፤ በኃጢአት መውደቁንና በዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር ቁጣና ፍርድ ያለበት በደለኛ መሆኑን ያምናል፡፡
ካውንስሉ ሰው በእግዚአብሔር አምሳል በመፈጠሩ አምላክ በሉዓላዊነቱ በሚያስተዳድረው ፍጥረት ውስጥ ምድርን የመጠበቅና የማልማት አደራና ኃላፊነት የተቀበለ ክቡር ፍጡር እንደሆነ፤ሰው በፍጥረቱ በዕውቀቱና በችሎታው ውስን የሆነ፤ መለኮትነት የሌለው፤መጽሐፍም እንደሚል “ከእግዚአብሔር ሕይወትና እስትንፋስ እየተቀበለ” የሚኖር በእግዚአብሔር ላይ ተደጋፊ ፍጡር እንደሆነ፤ ሰው ከምድር አፈር በመበጀቱና የእግዚአብሔር እስትንፋስ በውስጡ በመኖሩ ቁሳዊም፣ መንፈሳዊም ማንነት ያለው ፍጡር መሆኑን፤ ሰው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ወይም ትዕዛዝ ችላ በማለት የራሱን ፈቃድ በተከተለ ጊዜ በኃጢአት መውደቁና ኃጢአትም ወደ ምድር መግባቱን፤ከዚህም የተነሳ የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ቀውስ ጠብና መለያየት፤በሽታና ስቃይ ጭንቀትና መከራ ሞትም መከሰቱን፤ስለዚህም የእግዚአብሔር ቁጣና ፍርድ በኃጢአት ምክንያት በሰው ልጅ ላይ እንደደረሰ ያምናል፡፡
(ዘፍ 1፡26-27፤ ዘፍ 2፡7፤ ዘፍ 2፡21-22፤ ዘፍ 3፡16-19፤ ኢዮብ 10፡8፤ ኢዮብ 33፡4፤ መዝ 100፡3፤ ኢሳ 42፡5፣ 45፡12፤ ኤር 27፡5፤ ሐዋ.17፡24-27፤ ራዕይ 4፡11)
አዕማድ 4. የሰው ልጆች ድነት (መስቀለ ክርስቶስ – የድነት ጎዳና)
ካውንስሉ ሰው ከኃጢአት ዕዳ ኃይልና ቅጣት ሊድን የሚችለው ኃጢአት የሌለበት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ምትክ ሆኖ በመስቀል ላይ በፈጸመው የቤዛነት ሥራ ብቻ በመሆኑ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር ጸጋ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ እንደሚጸድቅ ያምናል፡፡
ካውንስሉ የሰው ልጅ በራሱ ሥራም ይሁን በሌሎች ፍጥረታት እርዳታ በኃጢአት ምክንያት ከመጣበት የእግዚአብሔር ቁጣ ሊድን ስለማይችል ድነት ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር ጸጋና ምህረት መሆኑን፤የክርስቶስ መስቀል የሰው ልጅ ድነት ሙሉ ለሙሉ የተከናወነበት ቦታ እንደሆነ፤ ክርስቶስ በመሞቱና በመነሳቱ የዘላለም ሕይወት ዋስትና መገኘቱን ያምናል፡፡
ካውንስሉ መስቀሉ የወንጌል ማዕከል መሆኑን፤የመስቀሉም መንገድ የኑሮአችን መርሕና ዘይቤ እንደሆነ፤ማለትም በመስጠት ማግኘት የሚስተናገድበት፤ከሁሉ ኋላ በመሆን ፊተኛ የሚኮንበት፤በድካም ብርታት የሚገለጽበት፤ስለዚህም በውርደት ክብር የሚለበስበት የሕይወት ቅኝት መሆኑን ያምናል፡፡
ካውንስሉ ሰው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሲያምን በመንፈስ ዳግም በመወለድ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሚሆን፤ አዲስ ፍጥረትም እንደሚሆን፤ ከእግዚአብሔር ፍርድና ቁጣ ድኖ የክርስቶስን ጽድቅ እንደሚጎናጸፍ ያምናል፡፡
ይህም አዲስ ፍጥረት በጽድቅና በቅድስና የተቃኘ አዲስ የሕይወት ዘይቤ ይከተላል፡፡ በዚህ ምክንያት መጽሓፍ እንደሚያስተምረው “መንፈሱም፣ ነፍሱም፤ ሥጋውም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለነቀፋ ፈጽሞ እንዲጠበቅ” በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ሁለንተናው በቅዱስ ኑሮ የተመራ ሰው እንደሚሆን ያምናል፡፡
ካውንስሉ እንደሚያምነው ኃጢአት አመጽ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ያለመታዘዝና ሕግን የመተላለፍ ተግባርም ነው፡፡ ኃጢአት ከእግዚአብሔር አሳብና ፈቃድ ውጭ የመሆን ኑሮ ነው፡፡ የኃጢአትም ደመወዝ ሞት ነው፡፡ ካውንስሉ በክርስቶስ አምኖ ዳግም የተወለደ ሰው ኃጢአት ሊያደርግና በኃጢአት ሊኖር እንደማይገባው ያምናል፡፡ ነገር ግን አማኝ ኃጢአት ቢያደርግ በእውነተኛ ኑዛዜና ንስሐ ወደ ጌታ ቢመለስ የክርስቶስ ኢየሱስ ደም ከኃጢአት ሁሉ እንደሚያነጻው ያምናል፡፡
(ኢሳ 53፡1-12፤ ዮሐ 3፡16፤ ሮሜ 3፡25፣ 8፡3-4፤ ኤፌ 2፡5-6፤ 1ተሰ 4፡2፤ ቲቶ 2፡11-15፤ 1ዮሐ 1፡7-10፣ 4፡10፣ 5፡23፤)
አዕማድ 5. ቤተ ክርስቲያን
ካውንስሉ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን በእግዚአብሔር መንፈስ ዳግም የተወለዱ አማኞች ሁሉ በሚገኙባትና የኢየሱስ ክርስቶስ አካል በሆነች በአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን ያምናል፡፡
“ቤተ ክርስቲያን” የሚለው ቃል ትርጉም የክርስቲያን ወገን ወይም የክርስቲያን ማኅበረሰብ ማለት ሲሆን ቃሉ በቁሙ ሲወሰድ ሕንጻን የሚያመለክት ቢመስልም በመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ ግን ቤተ ክርስቲያን ማለት ማህኅበረ ክርስቶስ እንደሆነ ያምናል፡፡
የቤተ ክርስቲያን መሥራች እና ጀማሪዋ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ፤ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ደም የተዋጀች፤በመንፈስ ቅዱስ ለቤዛ ቀን የታተመች፤በቃሉና በመንፈሱ እየነጻችና እየታነጸች የምትገሰግስ ሠራዊት መሆኗን ያምናል፡፡
ካውንስሉ ቤተክርስቲያን በክርስቶስ በተገለጠው የወንጌል እውነት ላይ የቆመች ይህንኑ የመዳን ወንጌል ለዓለም ሁሉ ልታውጅ በሕይወቷም ልትገልጸው የተጠራች ባለ ተልእኮ ማኅበረሰብ እንደሆነችና አገልግሎቷን በትህትናና በቅንነት እንዲሁም በተገቢው ሥርዓት ማከናወን እንዳለባት ያምናል፡፡
ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ አንድነት የምትመላለስ የጌታ እራትና ቅዱስ (የውኃ) ጥምቀት በሚባሉ ቅዱስ ሥርዓቶች አንድነቷን እየገለጸች፤ የቤተ ክርስቲያን ራስ ከሆነው ከክርስቶስ በተቀበለችው ሥልጣን ምዕመኗንን እያስተዳደረችና እየመራች በዓለም ከሚገኝ ዕድፍ ራሷን እየጠበቀችና በጎ ምግባርን እያበረታታች እስከ ጌታ ምጽአት ቀን ድረስ በዚህ ምድር የምትቆይ የክርስቶስ አካል እንደሆነችም ያምናል፡፡
እንዲሁም አማኞች የአምላካቸውንና የጌታቸውን የቸርነትና የበጎ ምግባር አርአያነት ተከትለው በምድር ተንሠራፍቶ ያለውን የሰውን ልጅ መንፈሳዊ፤ሥነ-ልቦናዊ፤ቁሳዊና ማኅበራዊ ኑሮ ሥቃይ የሚካፈሉ፤ችግሩን ለማቅለልም በቅን ልቡና የራሳቸውን ድርሻ የሚወጡ ሊሆኑ እንደሚገባቸው ያምናል፡፡ በቅዱስ ቃሉም ስለ ሥራ ትጋት የተሰጠውን መመሪያ ተቀብለው፤ በግልም ሆነ በኅብረት ለሥራ የተነቃቁ፤በታማኝነት እና በትጋት የሚያገለግሉ ሊሆኑ እንደሚገባ ያምናል፡፡
ካውንስሉ ጋብቻ በተቃራኒ ፆታዎች ማለትም በተፈጥሮ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚፈጸም ክቡር የአንድነት ኪዳን መሆኑን፤ ተጋቢዎችም በፍቅርና በታማኝነት ለእግዚአብሔር ክብር በቅድስና መኖር እንደሚገባቸው ያምናል፡፡
(ማቴ 16፡18፣ 25፡34-40፤ ሐዋ 20፡28፤ ሮሜ 12፡5 1ቆሮ 3፡11፣ 10፡16-17፤ 2ቆሮ 1፡22፤ ገላ 1፡8፣ 3፡28፤ እና 12፤ ፤ ኤፌ 4፡13፤ ያዕ.2፡14-17፤ ራዕ 1፡5፣)
አዕማድ 6. ቅዱሳን መላዕክትና የወደቁ መላእክት
ካውንስሉ እንደሚያምነው ቅዱሳን መላዕክት መንፈሳውያን ፍጥረት ሲሆኑ በእግዚአብሔር ፈቃድ የሚንቀሳቀሱ፤በምድር ላይ የእርሱን ዓላማ የሚያስፈጽሙ አገልጋዮች መሆናቸውን፤በእርሱ የሚያምኑትን ቅዱሳን ሰዎች ለማገልገል ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚላኩ፤ከሰው ልጆች ዕውቀትና ችሎታ በላይ ኃይል የተሰጣቸው በአምላክ ፊት የሚቆሙ ፍጥረት መሆናቸውን ያምናል፡፡
የወደቁ መላእክት የተባሉት የጨለማው ዓለም ገዢ በተባለው በመሪያቸው በዲያቢሎስ ወይም በሰይጣን አለቅነት የሚንቀሳቀሱ የክፋት መንፈሳዊያን ሠራዊት መሆናቸውን፤በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች ከዚህ ጨለማ ሠራዊት ጋር በብርቱ ጦርነት ውስጥ ያሉ መሆናቸውንና “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል” ባለው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ብርታት ድል ነሽዎች መሆናቸውን ያምናል፡፡
(ማቴ.28፡2-7፣18 ፤ ሉቃ.9፡1፣ 10፡17-20፤ ኤፌ.6፡10-18፤ ቆላ.1፡16፤ 1ጢሞ.3፡16፤ ዕብ.1፡14፤ 1ጴጥ.5፡8-9፣ 2ጴጥ.2፡4፣11፤ ይሁዳ 6፤ያዕ.4፡7)
አዕማድ 7. የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአትና የዓለም መጨረሻ
ካውንስሉ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ እንደ ሄደ እንደዚሁም በአካል ተመልሶ ወደ ምድር እንደሚመጣ፤ የሙታንም ትንሣኤ እንደሚሆን ያምናል፡፡
የእርሱ መምጣት የዓለም ታሪክ ፍጻሜ እንደሚሆን፤ በመጨረሻም ፍርድ ኃጥአን ወደ ዘላለም ቅጣት ሲሄዱ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው የሞቱት ተነስተው በመምጣቱም ጊዜ በሕይወት የሚኖሩ አማኞች ወደ ዘላለም ሕይወት እንደሚሄዱ ይህም ለአማኞች የተባረከና በንቃት ሊጠብቁት የተገባ ተስፋቸው እንደሆነ ያምናል፡፡
(ማቴ.24፡36-42፤ ዮሐ.14፡1-3፤ ሐዋ.1፡11፤ 1ተሰ.5፡2፤ ፤ ራዕ.19፡11-16፤ 20፡11-15፤ 22፡12-15)፡፡
Expert Agents

Robert Hendz
Commercial Real Estate

Loreen James
Residential Real Estate

Mike Brenson
Residential Real Estate

Brett Slater
Commercial Real Estate